Friday, May 23, 2014

‎ተውሂዱል ኡሉሒያ‬

  


“ኡሉሒያ” (አምላክነት) “ኢላህ” (አምላክ) ከሚለው ስም የተወሰደ ሲሆን የሚመለክና ትዕዛዙ ሊፈፀም የሚገባ ማለት ነው፡፡ “ኢላህ” (አምላክ) ከአላህ ውብ ስሞች አንዱ ሲሆን “ኡሉሂያ” (አምላክነት) ደግሞ ከታላቅ ባህሪያቱ አንዱ ነው፡፡
አላህ ልቦች ሊያመልኩት፣ ሊዋረዱለትና ትዕዛዙን ሊፈፅሙ የሚገባ አምላክ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጥረተ ዓለምን የፈጠረ፣ ጉዳዮችን የሚያስተናብር፣ በተሟሉ ባህሪዎች ሁሉ የተገለፀ፣ ከጉድለቶች ሁሉ የተጥራራ ትልቅ ጌታ ነው፡፡
መዋረድና መተናነስ ለርሱ እንጂ ለማንም አይገባም፡፡ በመፍጠር በማስገኘትና እንደነበር በመመለስ ብቸኛና ማንም ማይጋራው ስለሆነ በአምልኮም ማንም ሊጋራው ማይገባ ብቸኛ መሆኑ የግድ ነው፡፡

“ተውሂዱል ኡሉሂያ” አላህን በአምልኮ ብቸኛ ማድረግ ሲሆን ይህም የሚሆነው አንድ ባሪያ በትክክል መመለክ የሚገባው አላህ ብቻ መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ ሲያውቅ ነው፡፡ የመመለክ ባህሪ ከአላህ ሌላ ለማንኛውም ፍጡር እንደሌለ ሲያውቅ ውስጣዊና ውጫዊ በሆኑ የአምኮ ዘርፎች በሙሉ አላህን ብቸኛ በማድረግ እንደ ሰላት፣ ዘካ፣ ፆም፣ ሀጅ፣ በመልካም ማዘዝ፣ ከመጥፎ መከልከል፣ ወላጆችን መታዘዝ፣ ዝምድናን መቀጠልና የመሳሰሉትን አካላዊ አምልኮዎችንና እንደ በአላህ ማመን፣ በመላኢኮች፣ በመፅሐፎች፣ በመልዕክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በቀድር ማመን በመሳሰሉት ልባዊ እምነቶች አላህን ብቸኛ በማድረግ የአላህን ውዴታና የርሱን ምንዳ ብቻ በመከጀል ያመልከዋል፡፡
አላህን በብቸኝነት ማምለክ ግዴታ ስለመሆኑ ብዙና የተለየዩ ማሰረጃዎች አሉ፡-
1. አንዳንዴ በትዕዛዝ መልኩ ይቀርባል::
አላህ እንዲህ ይላል፦
‹‹ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡ (አል በቀራህ 21)

‹‹አላህንም ተገዙ፡፡ በእርሱም ምንንም አታጋሩ፡፡(አል ኒሳህ 36)
‹‹ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፡፡ (ኢስራህ 23)
ይህን የመሳሰሉ አንቀፆች ሌሎችም አሉ፡፡

2. አንዳንዴ ሰዎች ጋኔኖችና ሌሎችም ፍጥረታት የተገኙለት ዋነኛ ዓላማ ተደርጎ ይገለፃል:: አላህ እንዲህ ይላል፦
‹‹ጋኔንንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ (ዛሪያት 56)

3. አንዳንዴ ይህ የመልክተኞች መላክ አላማ ተደረጐ ይገለፃል፡፡ ለምሳሌ አላህ አንዲህ ይላል-
‹‹በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፡፡ (ነህል 36)

‹‹ከአንተ በፊትም እነሆ ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡ (አንቢያ 25)
እነዚህና ሌሎችም ተውሂድን የሚያፀድቁ ወደ እርሱ የሚጣሩ፣ ትሩፋቱን የሚገልፁ፣ የቤተሰቡን ምንዳና የተቃራኒዎችን አደጋ የማያብራሩ የማስረጃ አይነቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ኢንሻ አላህ ይቀጥላል...

 


No comments:

Post a Comment